top of page

የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሰው የገቡ 20 አውሮፕላኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ገለፀ።


የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሰው የገቡ 20 አውሮፕላኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ገለፀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፈቃድ ሳይኖራቸው የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሰው ሲበሩ የነበሩ 20 ቱሪስት አውሮፕላኖች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከትላንት በስቲያ አመሻሽ ላይ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሰው የገቡት እነዚህ አውሮፕላኖች በጋምቤላ አውሮፕላን ጣቢያ እንዲያርፉ ተደርጓል።

አውሮፕላኖቹ እያንዳንዳቸው ስንት ሰው እንዳሳፈሩ፣የየት አገር ዜግነት እንዳላቸውና የንብረት ባለቤቶቹ እነማን እንደሆኑ በምርመራ ላይ ይገኛል። በአለም አቀፉ የበረራ ህግ መሰረት ማንኛውም አውሮፕላን የአገራትን ሉአላዊነት በጣሰ መንገድ በየትኛውም አገር ላይ ማረፍ ወይም መብረር አይችልም።

አውሮፕላኖቹ ለምን ወደ ኢትዮጵያ የአየር ክልል እንደገቡ ሲጠየቁ ተገቢውን መልስ ባለመስጠታቸው በቁጥጥር ስር ውለው ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት። ከትላንት ጠዋት ጀምሮ የምርመራ ቡድን ወደ ጋምቤላ ክልል መላኩን ገልጸው ምርመራው እንደተጠናቀቀ መረጃው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የአውሮፕላኖቹ በቁጥጥር ስር መዋል ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር ይገናኝ ይሆን ተብሎ ለዋና ዳይሬክተሩ ለቀረበላቸው ጥያቄም "ይህ ጉዳይ የሉዓላዊነት ጉዳይ እንጂ ከአዋጁ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም" ብለዋል። ያለ ፕሮግራም ወደ ኢትዮጵያ አየር ክልል ገብተው ለማረፍ የሚፈልጉ አውሮፕላኖች በአዲስ አበባ ብቻ ማረፍ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ አቪዬሽን አሰራር የሚያስገድድ ሲሆን ከዚህ ውጭ የሚደረጉ በረራዎች ግን ክልክል ናቸው። ከዚህ በፊት ያለ ፍቃድ ወደ ኢትዮጵያ አየር ክልል የገባ አውሮፕላን አጋጥሞ እንደማያውቅ የጠቀሱት ኮለኔል ወሰንየለህ ይህ ሲከሰት የመጀመሪያው መሆኑን አስረድተዋል። ዓለም አቀፉ የበረራ ህግ በሚያዘው መሰረት ምርመራ እየተደረገ ሲሆን በአውሮፕላኑ ውስጥ የተገኙ ዜጎችም ጥበቃና ክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል ተብሏል።


Who's Behind The Blog
Recommanded Reading

Search By Tags

No tags yet.

Follow  ''ethiodailypost''

  • Facebook Social Icon
  • Twitter Social Icon
  • Google+ Social Icon
  • Instagram Social Icon
  • YouTube Social  Icon
  • RSS Social Icon
bottom of page